ስለ ‘እብዷ ኢንተርፕርነር’ ካቲ (የመጨረሻ ክፍል-2)

በዚህ ወቅት ካቲ ወደ ሌላ ስፍራ ስራ ፍለጋ ለመሄድ አልተነሳችም፡፡ወደ ሲያትልም አልተመለሰችም፡፡እዚያው ኒውዮርክ ዉስጥ Kazzy & Associates የተባለ የምግብና የመጠጥ አዘገጃጀት ጉዳይን የሚያማክር ድርጅት ከፈተች እንጅ፡፡

በ1989 ዓ/ም ካቲ በሲያትል የሚገኝ አንድ ጥንታዊ ህንጻ ገዝታ በማደስ እዚያም ስራ ጀመረች፡፡ስሙ ግን የቀድሞው አይደለም፡፡ ካቲ ካሴይ የምግብ ስቱዲዮ/ Kathy Casey Food Studio/ ይባላል፡፡ይህ ድርጅት ምግብና መጠጥን በሚመለከት አዳዲስ ሃሳቦች የሚፀነሱበት ነው፡፡ ምክርና ሃሳብ በመሻት ወደዚህ ድርጅት የሚሄድ ሁሉ ጠቀም ያለ ገንዘብ መያዝ ያለበት ሲሆን በምትኩ በከፊል ያደገ የቢዝነስ ሽል ይዞ ወደመጣበት ይመለሳል፡፡ ይህንን ሽል ይዞ የሄደው ሰው ህልሙን በምጥ ሳይሰቃይ እዉን ያደርጋል ማለት ነዉ፡፡ በመሃከል ሽሉ እክል ሳይገጥመዉ ይወለድ ዘንድ እነ ካቲ ክትትል አይነፍጉም፡፡

በ2002 ዓ/ም እንደገና Dish D’Lish Cafes & Specialty Products የተባለ አዲስ ቢዝነስ የከፈተችው ካቲ “ለመሆኑ” ትላለች “ለመሆኑ እራት ለመብላት ወጣ ብለህ በምግቡ ጣእም ቅር ተሰኝተህ ታውቃለህ? እግዚአብሔርን ነው የምልህ ምግቡ ያልጣመህ ያን ምግብ ያበሰለው ሰው ያን ምግብ መስራት ስለማይወድ ነው፡፡ከምግብ እኮ ጣዕምን የምታገኘዉ ስለሚሰሩት ምግብ ዋጋ ከከፈሉ ሰዎች ነዉ፡፡ስለምግብ አሰራር የሚጨነቅ ሰው ጣዕምን የሚፈጥረዉ ተመጋቢን ለማስደሰት ብቻ ሳይሆን ለእራሱም ደስታ ስለሚፈጥርለት ነው፡፡ምክንያቱም ነፍሱ የተፈጠረችው ለዚያ ነዋ!”

ከሃያ ዓመታት በኋላም ካቲ አዳዲስ የምግብ ዝርያዎችን ማስተዋወቋን ተያይዘዋለች፡፡ ካቲ እንደምትለው ፈጠራ የሚመጣው ስለምትፈጥረው ነገር ስትጨነቅና ስታስብበት ነዉ፡፡ አንተ ላንድ ነገር ተነሳሽነቱ እና ፍላጎቱ ካለህ ይኼ በራሱ ስለምትመኘው ነገር በደንብ ወደምታውቅበት መስክ ይወስድሃል፡፡ከዚያ መስክ የቻልከውን ያህል ልምድ እና እዉቀት የመቅሰም እድል ታገኛለህ፡፡ህልምህ ያንተና ከዉስጥህ ከሆነ አሁንም ወደፊት ለመሄድ በመስኩ ላይ መተኛት እንደሌለብህ በዚያ ያገኘኸው ትምህርት ይነግርሃል፡፡ስለዚህ ወደፊት…ወደፊት…ትሄዳለህ፡፡ አሁንም በጉዞህ ውስጥ በርካታ ነገሮችን ትማራለህ…ሌላም ትፈልጋለህ፡፡ ይህ ፍለጋ ነው ወደ ፈጠራ የሚያደርስህ፡፡ እኔ እዚህ የደረስኩት በዚህ መልኩ እየወደቅሁ እየተነሳሁ እንጅ በማመንታት አይደለም፡፡

ካቲ ምግብ ነክ ጉዳዮችን እና የምግብ አሰራር ጥበብን የሚተነትኑ በርካታ መጽሃፍትን ከማዘጋጀቷም በላይ ጽሁፎቿ በበርካታ መጽሄቶች ላይ ታትመውላታል፡፡ላሪ ኪንግ ላይን፤ጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ፤እና ዘ ፉድ ኔትዎርክ በተሰኙት ሚዲያዎች ስለማያልቀው ፈጠራዋ ሽፋን በማግኘት  በተደጋጋሚ ቀርባለች፡፡

Thank you for your comments

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.