የቀድሞዋ የሶቬት ህብረት አካል የነበረችው ዩክሬን ከሶቬት ህብረት ከተገነጠለች በኋላ እንደዛሬው መጥፎ ቀን ገጥሟት አያውቅም። USATODAY እንደዘገበው የዩክሬን ዋና ከተማ ኬቭ በተቃዋሚዎች በሚቀጣጠሉ ጎማዎች ጭስ እና በፖሊስ ጥይት ባሩድ እየታጠነች ነው።
ከትናንት ሌሊት አንስቶ እስካዛሬ ድረስ በዘለቀው የተቃዋሚዎች እና የጸጥታ ሃይሎች ግጭት እስካሁን 241 ሰዎች ሲቆስሉ 37 ያህሉ ደግሞ እስከወዲያኛው አሸልበዋል። ከሞቱት ውስጥ ሃያ ስድስቱ ተቃዋሚ ሰልፈኞች፣አስሩ ፖሊሶች የተቀረው አንድ ደግሞ ጋዜጠኛ መሆኑን የዩክሬን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች በበኩላቸው ለሚቃወሟቸው ዩክሬናዊያን ከእንግዲህ ምንም ዓይነት ትዕግስት እንደሌላቸው እና ማንኛውንም ኃይል በመጠቀም እንደሚደመስሷቸው ዝተዋል።
የዩክሬን የጸጥታ እና ደህንነት ኤጀንሲ ሃላፊ የፕሬዝዳንቱን አቋም በሚያንጸባርቀው መግለጫቸው ከ1500 በላይ የጦር መሳሪያዎች ከተቃዋሚዎች እጅ ላይ መገኘታቸውን እንዲሁም በመላው ሃገሪቱ ‘ሽብርተኞች’ ያሏቸውን ተቃዋሚዎች የማጽዳት ዘመቻ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ ላለፉት ወራቶች በዋና ከተማዋ ኬቭ የተቃዋሚዎች መሰብሰቢያ የነበረውን አደባባይ የዩክሬን የጸጥታ ሃይሎች በሁለት ብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪ በመታገዝ ጥሰው ለመግባት ሲሞክሩ ነው የትናንቱ ግጭት የተከሰተው:: በውጤቱም ብዙዎች ሲቆስሉ ብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎቹ ግን የእሳት ሲሳይ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት እርምጃ የተቆጡ ሰልፈኞች በየቦታው መሰብሰቢያ አድርገዋቸው የነበሩትን በርካታ የመንግስት ህንጻዎች፣የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ህንፃ እና ዋና ከተማዋ መሃል የሚገኘውን ትልቁን የንግድ ማህበራት ጽ/ቤት ህንፃ እንደ ጧፍ አንድደዋቸዋል።
በቁማቸው በእሳት የተያያዙ ሰዎችም ታይተዋል።
ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ወቅት ወደ ዋና ከተማዋ የሚተሙ ተቃዋሚዎች መብዛት መንግስትን ያስደነበረው ሲሆን ወደዋና ከተማዋ የሚወስዱ የባቡር መስመሮችን እና ጎዳናወችን በመዝጋት ሰልፈኞች ኬቭ እንዳይደርሱ ለማድረግ በመጣር ላይ ይገኛል። ወትሮውንም ቢሆን መንግስት ከራሽያ ጋር አለኝ የሚለው ወዳኝነት የማይዋጥላቸዉ የምእራብ ዩክሬን ነዋሪዎች ለቪቭ ከተባለች ከተማ ተነስተው ጸረ መንግስት ሰልፉን ለመቀላቀል ወደ ኬቭ በማቅናት ላይ ሳሉ መሃል መንገድ ላይ በፖሊስ ታግተዋል።
የዩክሬን ተጠባባቂ መከላከያ ሚንስትር ፓቭሎ ሌቤዴቭ ከITAR የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ተወርዋሪ የጦር ሰራዊት በዋና ከተማዋ አቅራቢያ ማስፈራቸውን ያመኑ ሲሆን ‘ሰልፈኞችን ተኩሳችሁ ግን ግደሉ አላልኩም’ በማለት ከደሙ ንጹህ ነኝ ለማለት ሞክረዋል። በቅርቡ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስቴር መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ በመቃወም ስልጣን መልቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን የእሳቸውን ስልጣን መልቀቅ ተከትሎም ፕሬዝዳንቱ የመንግስታቸውን ካቢኔ ለመበተን ተገደዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖሊሶች ‘ከመጠን ያለፈ ሃይል ተጠቅመዋል’ በማለት የአውሮፓ ህብረት የዩክሬን መንግስት ባለስልጣናትን በማዕቀብ ለመቅጣት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆሴ ማኑዬል ባሮሶ አስታውቀዋል። የ28ቱ የአውሮፓ ህብረት ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮችም ‘ልዩ’ ላለው አስቸኳይ ስብሰባ ወደ ብራሰልስ እንዲመጡ ህብረቱ ጥሪ አስተላልፏል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ሆላንዴ የዩክሬን መንግስት በዜጎቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ ‘ተቀባይነት የሌለው እና ሊታገሱት የማይቻል’ ብለውታል።
የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርል ቢልት በበኩላቸው ‘ዛሬ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት እጅ በደም ተጨማልቋል!’ ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የራሻው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቃል አቀባያቸው ዲምትሪ ፔስኮቭ በኩል ‘በዩክሬን መፈንቅለ መንግስት እያካሄዱ ነው’ ያሏቸውን ምእራባዊያን አውግዘዋል። ‘ዛሬ ሩሲያ ለዩክሬን ልትሰጣት የነበረውን የ2 ቢሊዮን ዶላር እርዳታም የዩክሬንን መፃዒ እድል እስከምናውቅ ድረስ በእጃችን ይቆያል’ በማለት ፔስኮቭ የክሬሚሊንን አቋም ግልጽ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች አፍቃሬ አውሮፓ ዩክሬናዊያን ተቃዋሚዎቻቸውን እስከመቼ ይገዳደሩ ይሆን?
ዩክሬንን የሚመለከቱ አዳዲስ ዜናዎች
>>ሃያ የዩክሬን መንግስት ባለስልጣት ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣሏን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
>>የአውሮፓ ህብረት ለጊዜው በግልጽ ይፋ ያላደረገውን ማዕቀብ እንደጣለም በውጭ ጉዳይ ሃላፊዋ ወ/ሮ ካትሪን አሽተን በኩል አስታውቋል።
>>ኦስትሪያ በሃገሯ የዩክሬን መንግስት ባለስልጣት ያከማቹትን ገንዘብ በተናጥል እንደምታግድ የፋይናን ሚንስትሩ ቃል አቀባይ ሶንጃ ስቴስል ለኦስትሪያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
>>ከምእራብ ዩክሬን ለቪቭ ከተማ የተነሱ በርካታ የዩክሬን ወታደሮች መንግስትን በመክዳት ዋና ከተማዋ ኬቭ በሚገኘው የነጻነት አደባባይ የተቃውሞውን ጎራ መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል።
>>የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች በበኩላቸው አስቸኳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።