ናዚዝም የሚለው የጀርመንኛ ቃል በእንግሊዝኛ ናሽናል ሶሻሊዝም ማለት ነው።የዚህ ሶሻሊስታዊ ብሄርተኝነት ፊታውራሪ ደግሞ የጀርመን ብሄራዊ ሰራተኞች ፓርቲ ሊቀመንበር የነበረውና የሃገሪቱ መሪ ሆኖ መንበረ ስልጣኑን የጨበጠው አዶልፍ ሂትለር ነበር። በአዶልፍ ሂትለር የሚመራው ናዚ ብሄርተኝነት ያሰከራቸው ዘረኛ ሶሻሊስቶች በመንግስት ስም ተደራጅተው ንጹሃንን በሽብር መረብ እያጠመዱ የፈጁበት የነፍሰ ገዳዮች ስብስብ ነበር።በጀርመን ናዚዝም ማለትም የማያውቁትን ሃገር እና ህዝብ የመናቅና የጥላቻ ሶሻሊስታዊ ብሄርተኝነት ስሩን ሰደደ። ናዚ የሶሻሊስቶች ስብስብ ሲሆን ስሙን ያገኘውም ‘ናሽናል ሶሻሊስት ጀርመን ወርከርስ ፓርቲ’ ከሚለው መጠሪያቸው ነው።
የናዚ ዋና መመሪያ እና መሪ ቃል “ሄል ጀርመን!” ነው። ‘ጀርመን ትቅደም!’ እንደማለት ነው።ለነገሩ የኢትዮጵያ ትቅደምም ምንጭ ከዚያው ሳይሆን አይቀርም። ሌሎችን በጦርነት በማፈራረስ እና ሰዎችን በመፍጀት ባይሆን ኑሮ መቅደም ባልከፋ ነበር። ናዚ ጀርመንን አስቀድማለሁ በማለት አያሌ ሚሊዮኖችን ፈጅቷል። የቀድሞዋ ሶቬት ህብረት የዩክሬን ግንባር ጦር ሰራዊት ካምፑን ነጻ ባወጣበት ወቅት 348,820 ሽህ የወንዶች ልብስ እና 836,525ሽህ የሴቶች ልብስ በመጋዘን አግኝቷል። በተጨማሪም 516,843ሽህ የወንድና የሴት ልብሶች ወደ ጀርመን መጓጓዛቸውን የሚገልጽ ማስረጃም አግኝቷል። የሰዎቹን ቁጥር እንግዲህ ደምሩና ድረሱበት። ልብሶቹ ወደ ጀርመን ከተላኩ በኋላ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካወች እንደ አዲስ ተሰርተው ለገበያ ይቀርባሉ።
ናዚ እነዚህን ሰዎች ከመግደሉ በፊት “ሻወር ልትወስዱ ስለሆነ ልብሳችሁን አወላልቁ።” ብሎ ያዛል። የዋህ ንጹሃን እውነት መስሏቸው ልብሳቸውን ካወላለቁ በኋላ የሚገቡት የውሃ ሻወር ሳይሆን የዛይክሎን መርዝ ጋዝ በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ነበር። ይችን የሞት ሻወር ቀልቡ/ቧ ነግሮ/ሯት መውሰድ ‘አልፈልግም’ የሚል ወይም የሚያንገራግር እስረኛ ወዲያውኑ በጥይት ይገደላል። በብሄርተኛ ሶሻሊዝም የሰከሩት የነፍሰ ገዳዮች ቡድን ናዚ እስረኞችን ከገደለ በኋላ በኦሽዊትዝ ካምፕ ውስጥ ከታች በፎቶው በምታዩት ምድጃ ይከትና በእቶን እሳት በማክሰል ወደ ትቢያነት ይቀይራቸዋል።
ናዚ የወርቅ ጥርስ ያላቸውን እስረኞች ከገደለ በኋላ ወደ እሳት ምድጃው ከማስገባቱ በፊት ጥርሳቸው በመሮ እንዲወልቅ ያደርጋል። ናዚ በዚህ መልኩ በቀን እስከ 10ኪሎ ወርቅ ይሰበስብ ነበር። ይህ ወርቅ በደንብ ሲከማች ለጀርመን ብሄራዊ ባንክ ተልኮ በዚያ ለገበያ ይቀርባል። የሴት እስረኞች ጸጉር እና ከ20ሚሊሜትር ከፍ የሚል ጸጉር ያላቸው ወንዶች ሁሉ ጸጉራቸው ይላጭና በጆንያ ተሞልቶ ወደ ጀርመን ይላካል። በዚያ ዘመን የናዚ ወታደሮች የሚያደርጉት ካልሲ ከነዚህ ሰዎች ጸጉር የሚሰራ ነበር። የኦሽዊትዝ ካምፕ ነጻ በወጣበት ጊዜ ከ7000ሽህ ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ጸጉር በመጋዘን ተገኝቷል። ወንድ እስረኞችን በጨረር፣ሴቶችን በመርፌ ማምከን ለናዚ መዝናኛ ነበር። ብሄርተኛ ሶሻሊስቶቹ ናዚዎች እንደ ህጻን ልጅ የሚጠሉት እና የሚጠየፉት ነገር አልነበረም። በዚህ ካምፕ ከወላጆቻቸው ጋር ተይዘው የሚገቡ ህጻናት የሚገደሉት ወዲያውኑ ነበር። አብዛኞቹን በእሳት ምድጃ ውስጥ የሚከታቸው ከነ ህይወታቸው ነው። ናዚ የተወለዱትን ብቻ ሳይሆን በማህጸን ያሉ ልጆችንም አይወድም። ስለዚህም እርጉዝ ሴቶችን እንደ ህጻናቱ ሁሉ ወዲያውኑ ይገድላቸው ነበር።
በየሃገሩ ይህን መሰል እና ሌሎች ዘግናኝ ሰቆቃዎችን እንዲፈፅሙ ኢንሰንቲቭ የሆናቸው ሶሻሊዝም እንኳን ለሰው ልጅ ለእንስሳት አስተዳደርም የማይገባ የአካይስቶች እና የዘረኞች ስርዓት ነው። ብሄርተኛ ሶሻሊዝም/ናዚዝም እንዴት መራዥ የሆነ አስተሳሰብ እንደሆነና ያሁኗ ኢትዮጵያ ምን ያህል ለዚያ ቅርብ እንደሆነች ለማወቅ የካርል ማርክስን አስሩን የኮምዩኒስት መመሪያ ህግጋት (የሶሻሊዝም አስርቱ ቃላት) ያንብቡ።
ረሃብ ሌላው የናዚ መግደያ መንገድ ነው። የቅርብ ጊዜ የሞት ድግስ ለሌለባቸው እስረኞች ከብዙዎቹ መሃል እየመረጠ ዳቦ ይሰጣል።ታዲያ ብዙዎቹ ዳቦውን ደክመው ለሚያጣጥሩ ሰዎች ያካፍላሉ። በናዚ ዘንድ እንዲህ ያለ መተሳሰብ ወዲያው እና እዚያው እስር ቤቱ ክፍል ውስጥ የሚያስገድል ወንጀል ነው። የእነዚህ ሰዎች ጠኔ ካምፑ ነፃ በወጣ ጊዜ እንኳ ከካምፑ ለመውጣት የሚያስችል ጉልበት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። እነዚህ ሰዎች እስኪያገግሙ ድረስ ሰባት ያህሉ የዚህ ካምፕ ህንጻዎች በሆስፒታልነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። የኦሽዊትዝ ካምፕ በምታዩት መልኩ በሁለት ረደፍ ሆኖ ከፍተኛ ቮልቴጅ በሚሸከም የኤሌክትሪክ አጥር የታጠረ ነው።ከዚህ ማምለጥ እጅግ ከባድ ነው።
[በልዩ ሁኔታ ካልተጠቀሰ በቀር ዘመኖቹ በሙሉ እንደ ኤሮፓዊያን አቆጣጠር(እኤአ) ናቸው።