ካርል አማርኛግንቦት አምስት ቀን በአስራ ስምንት አስራ ስምንት ዓ/ም የተወለደ ጀርመናዊ ፈላስፋ እና አብዮተኛ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ ይኖራል ብየ አልጠረጥርም። ሙሉ ስሙ ነው። ካርል ሄነሪ ማርክስ ይባላል። ካርል ማርክስ ምጡቅ ጭንቅላት የነበረው ሰው መሆኑ ማንንም እንደማያከራክረው ሁሉ ከልጅነቱ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ከራሱ ጋር የተጣላ እና አይምሮው ያልተረጋጋ ሰው እንደነበርም እንደዚሁ ጥያቄ አያስነሳም። ካርል ማርክስ ቡርዣ የሚጠላ ግን በቡርዣ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ፣ ካፒታሊዝምን ለቴክኖሎጅ እድገት እና ለሃብት ፈጠራ የተመቸ ብሎ ካሞገሰ በኋላ በካፒታሊዝም ስር የሚኖረውን ማህበረሰብ ግን በዝባዥ ሲል የኖረ፣ እራሱን የሰራተኛው መደብ ቻርለስ ዳርዊን (ፈጣሪ እንደ ማለት) አድርጎ የሚያይ እና ለላብ አደሩ ሁልጊዜ የሚያስብ ነገር ግን በህይዎት ዘመኑ ሁሉ ቋሚ ስራ ያልነበረው እና ስራ የሚጠላ፣ ጅዎችን አጥብቆ የሚጠላ ነገር ግን በእናቱም በአባቱም ጅው የሆነ፣ የሃይማኖትን አይረቤነት እና አላስፈላጊነት ሲሰብክ የኖረ እራሱ ግን ከጁዳይዝም ወደ ሉተራን የክርስትና እምነት ቀይሮ የተጠመቀ፣ በዝባዥ የሚለውን ካፒታሊዝም ሲያጣጥል የኖረ፣ እርሱ ግን እድሜ ልኩን በድጎማ የኖረ እንዲሁም በዙሪያው የነበሩትን ሰዎች ሁሉ ሚስቱን እና ልጆቹን ጭምር ሲበዘብዝ የኖረ ሰው ነው።

ካርል ማርክስ ‘ዘ ዩኒየን ኦፍ ፌይዝፉል ዊዝ ክራይስት’ በሚል ጽሁፉ ፈጣሪን ስለመፍራት ጽፏል። ‘ኦን ዘ ጅዊሽ ኩዌሽን’ የሚለው ጽሁፉ ደግሞ ጸረ-ጅውነቱን የገለጠበት ሲሆን እኤአ በአስራ ስምንት አርባ ሶስት ዓ/ም በፓሪስ ጋዜጣ ላይ አውጥቶታል። ማርክስ ‘አዲሲቱ እየሩሳሌም’ የምትመሰረተው በማርክሲዝም ሶሻሊስታዊ አብዮት ብቻ እንደሆነ በጽሁፉ ላይ አትቷል። ካርል ማርክስ በስደት ላይ ሳለ በጋዜጣ ላይ በሚያወጣቸው ጽሁፎቹ ጀርመን ውስጥ አመፅ እየቀሰቀሰ ስላስቸገረ ከፈረንሳይ ተይዞ እንዲባረር ተደረገ። እናም ወደ ቤልጀም አቀና። በፈረንሳይ ፓሪስ ሳለ ከረጅም ጊዜ ወዳጁ ፍሬደሪክ ኤንግልስ ጋር ከመተዋወቁም በላይ ከቡርዣ ቤተሰብ ከተወለደችው ሚስቱ ጋርም መጋባት ችሏል።

“ዘ ጄነራል” በሚለው ልዩ ስሙ የሚታወቀው ፍሬደሪክ ኤንግልስ እስከ ማርክስ እለተ ሞት ድረስ ኑሮውን ሲደጉም እና ስራውን በገንዘብ ሲደግፍ የኖረ ከሃብታም ጀርመናዊያን ቤተሰብ እንግሊዝ ውስጥ የተወለደ በሴት አውልነቱ የሚታወቅ ቱጃር ነበር። ካርል ማርክስ በቤልጀም ስደት ላይ ሳለ በፍሬደሪክ ኤንግልስ ገፋፊነት እና ደጋፊነት እኤአ በየካቲት ወር አስራ ስምንት አርባ ስምንት ዓ/ም ዘ ኮምዩኒስት ማኒፌስቶ የተባለውን አብዮታዊ የሶሻሊዝም መመሪያ ጻፈ። የዚህን ጽሁፍ ህትመት ተከትሎ በፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያ እና ጣሊያን ሰራተኞች እና ላባደሮች አመጹ። ካርል ማርክስ በስደት በሚኖርበት ቤልጀምም ሰራተኞችን ማሳመጽ ብቻ ሳይሆን ከአባቱ በወረሰው ስድስት ሽሕ የወርቅ ፍራንክ የጦር መሳሪያ ገዝቶ መሳሪያ ሲያስታጥቅ ይደረስበትና እኤአ እስከ አስራ ስምንት አርባ ዘጠኝ ዓ/ም ድረስ ወህኒ ይወረወራል። እስሩን እንደጨረሰ ወደ ሃገሩ የተባረረው ማርክስ በዚያው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ሃገሩ ጀርመንም አሳደደችው።

ካርል ማርክስ ከሃገሩ ጀርመን እንደተባረረ ያቀናው የበርካታ ቡርዣዎች መኖሪያ ወደ ነበረችው ለንደን ነበር። በለንደን መጽሃፍትን ሲያነብ፣ ሲመራመርና ሲጽፍ የኖረው ማርክስ እኤአ በአስራ ስምንት ስልሳ ሰባት ዓ/ም “ዳስ ካፒታል” የተባለውን መጽሃፍ በጀርመንኛ ጽፎ በጓደኛው ፍሬደሪክ ኤንግልስ አማካይነት ለህትመት በቃ። ይህኛው ስራው ነባሩን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፍልስፍና ቢያንስ ለመቶ ያህል አመታት ጨለማ ውስጥ የከተተ ነበር። ካርል ማርክስ በዳስ ካፒታል ከዚያ በፊት ያልነበሩ በርካታ ቃላትን የተጠቀመ ሲሆን ከነዚያ ቃላቶች ውስጥ አምርሮ የሚኮንነውን ካፒታሊዝም ሳይቀር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው እና ቃሉንም የፈጠረው እራሱ ነው። ይሁን እንጅ ካፒታሊዝም ከአዳም ስሚዝ “ዘ ዌልዝ ኦፍ ኔሽን”ጋር እንዳልተወለደው ሁሉ በካርል ማርክስ “ዳስ ካፒታል”ም ሊሞት አልቻለም።

           ⦿ ካፒታሊዝም እና ዳስ ካፒታል 

ካርል ማርክስ በ ‘ዳስ ካፒታል’ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሞዴል ፍልስፍናዎችን ለማስተዋወቅ እና የካፒታሊዝምን ስርዓት ‘በዝባዥነት’ ለማስረዳት ሞክሯል። ማርክስ የማይለወጥ ሳይንሳዊ ህግ ባለው ሞዴሉ የካፒታሊዝም ስርዓት በእንከን የተሞላ፣ ካፒታሊስቶችን እና ትላልቅ ቢዝነሶችን ብቻ የሚጠቅም፣ ሰራተኞችን የሚበዘብዝ እንዲሁም መጨረሻ ላይ እራሱን የሚያጠፋ ስርዓት በመሆኑ መወገድ እና በኮምዩኒዝም መተካት አለበት ይላል። ማርክስ በ ‘ዳስ ካፒታል’ ላይ ካፒታሊዝም ለቴክኖሎጅ መስፋፋት ምቹ መሆኑን ይገልጽና ቴክኖሎጅ መስፋፋቱ ግን ማሽነሪዎች ሰራተኛውን ከስራ ውጭ በማድረግ ስራ አጥ ያደርጉታል ይላል። የሃገሩ ልጅ እና የኒዎ-ሊበራሊዝም አባት አሌክሳንደር ሩስቶ ይህን ምልከታውን በመጋራት “ቴክኖሎጅ የሰውን ልጅ አርቲፊሻል ብልፅግና በማላበስ ሰብዓዊነቱን ያጓድልበታል።” በማለት ተናግሯል።

ካርል ማርክስ የሰራተኛውን ጉልበት እና ዋጋ አስመልክቶ በ“ዳስ ካፒታል” ላይ ያሰፈረው ሃሳብ ከእሱ በፊት የኖረው እንግሊዛዊ ኢኮኖሚስት ዴቪድ ሪካርዶ አመለካከት ነጸብራቅ ሲሆን ሁለቱም “የሰራተኛ ጉልበት የምርትን ዋጋ ይወስናል።” የሚል የተንሸዋረረ ሃሳብ ይጋራሉ። እስካዛሬ ምድር ላይ ከነበሩ እና ካሉ ኢኮኖሚስቶች ሁሉ በሃብት የሚስተካከለው የሌለው ዴቪድ ሪካርዶ ከካርል ማርክስ ቀደም ብሎ የክላሲካል ኢኮኖሚክስ ፍልስፍናን መንገድ ያሳተ ነው።

ማርክስ ሰራተኛውን የዋጋ ሁሉ ቁልፍ በማድረግ ስለትርፍ እና ወለድ ደግሞ እንዲህ ይለናል። በመጀመሪያ ትርፍንም ሆነ ወለድን ማርክስ ጠቅለል አድርጎ እራሱ በፈጠረው ቃል ‘ሰርፕለስ ቫልዩ’ ሲል ይጠራቸዋል። ይህን በሂሳብ ስሌት ሲያስቀምጠውም ፕሮፊት(ፒ)=ሰርፕለስ ቫልዩ(ኤስ)/ፕሮዳክት(አር) በማለት ለምሳሌ በአንድ መቶ ብር ጃኬት የሚሸጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለሰራተኛው ጉልበት ሰባ ብር ያወጣ ከሆነ ትርፉ ፒ=ሰላሳ/መቶ=ዜሮ ነጥብ ሶስት ወይም ሰላሳ በመቶ ነው ይላል። ካርል ማርክስ የቢዝነስ ትርፍን ብዝበዛ ሲል ይጠረዋል። ይህ ተራ የሚመስል የካርል ማርክስ ስሌት በዚያ ዘመን ለነበሩ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ትልቅ ዱብዳ እና ገደል ሆኖባቸው ቆይቷል።

ከአዳም ስሚዝ እስከ ጆን ስቱዋርት ሚል ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖ የኖረው እና ኋላም ላይ በማርክስ እንቆቅልሻዊ ሂሳብ ጥያቄ ውስጥ የገባው የዋጋ(ቫልዩ) ምንነት እኤአ በአስራ ስምንት ሰባ አንድ ዓ/ም በሶስት የተለያዩ ኢኮኖሚስቶች ምላሽ አገኘ። የሶስቱም ምላሽ በ“ማሪጅናል ዩቲሊቲ ሪቮሉሽን” ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን በዚህ ቲዎሪ መሰረት ‘ዋጋ’ን የሚወስነው የሰራተኛው ጉልበት ሳይሆን የተጠቃሚ ፍላጎት መሆኑ ታወቀ። ካርል ማርክስ የፈጠረው ትልቅ ገደልም በእዚህ መልኩ ትልቅ ድልድይ ተበጀለት። ኢኮኖሚክስ ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደ ባዮሎጅ ወይም ኬሚስትሪ ወይም ደግሞ ፊዚክስና ሂሳብ ወጥ ሳይንስ መሆኑ አከተመ።

        ⦿ የካርል ማርክስ ስብዕና እና የቤተሰቡ አሳዛኝ ፍጻሜ!

ካርል ማርክስ ጠጭ፣አጫሽ እና እጅግ ሲበዛ ደንታ ቢስ የነበረ ሲሆን የውስጥ ልብሶቹን ሳይቀር የማይቀይር፣የቤቱ ወለል በሲጋራ ትርኳሽ እና የጣቶቹ ጥፍርም በቆሻሻ የተሞሉ እንደነበሩ በአንድ ወቅት በቤቱ ብርበራ ያደረጉት የፈረንሳይ የፖሊስ ባለስልጣናት ገልጸዋል። ማርክስ ሶስት ህጻናት ልጆቹ በራብ ሲሞቱ በዓይኑ እያየ ስራ ሰርቸ ላብላቸው ያላለ ሰው ነው። ማታ ማታ ሚስቱ ዳቦ ይዞ ይመጣል ብላ ስጠብቅ እሱ ሁልጊዜ አዳዲስ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና አገኘሁ እያለ ይተርክላት ነበር። ስለቤተሰብ ሲናገር ለሚሰማው ግን አፍ ያስከፍታል።ካርል ማርክስ በፍሬደሪክ ኢንግልስ ብቻ ሳይሆን በሁለት ትላልቅ ልጆቹ ይጦር ነበር። ማርክስ ከቤት ሰራተኛው ፍሪዲ የሚባል ወንድ ልጅ ወልዶ የካደ ሲሆን በቤተሰቡ በተነሳበት አታካራ ፍሬደሪክ ኤንግልስን አሳምኖ የኔ ልጅ ነው እንዲልለት አድርጓል።የማርክስ ኑሮው ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡ ፍጻሜም አሳዛኝ ነው። ሚስቱ እኤአ በ1881ዓ/ም በካንሰር ከሞተች ከሁለት ዓመት በኋላ በችጋር እና ስፍር ቁጥር በሌለው የበሽታ መዓት ተሰቃይቶ መጋቢት 17ቀን 1883ዓ/ም እስከወዲያኛው አሸለበ። ለመቀበሪያ የሚሆን ገንዘብ እንኳ ያልነበረው ማርክስ ወዳጁ ፍሬደሪክ ኢንግልስ ነው ያስቀበረው። በቀብሩ ላይም 20የሚሆን ሰው እንኳ አልተገኘም። ከዚህ በተጨማሪ ፍሬደሪክ ኤንግልስ ማርክስ ጀምሮ የተዋቸውን የዳስ ካፒታል ክፍል ሁለትና ሶስት መጽሃፍት ጨርሶ ለህትመት አብቅቶለታል። ፍሬደሪክ ኤንግልስ እኤአ በ1895ዓ/ም ሲሞት ፍሪዲ የተባለው ልጅ ማርክስ ከሰራተኛው የወለደው እንጅ የእውነት ልጁ እንዳልሆነ በኑዛዜው ላይ ተናግሯል። ኢሊያኖር የምትባለው የማርክስ ሴት ልጅ እኤአበ1898ዓ/ም ፍሪዲ ማርክስ ከሰራተኛቸው የወለደው ወንድሟ መሆኑን ስታውቅ ሩጣ አንገቷን ገመድ ውስጥ ከተተች። ቆንጆዋ ላውራ ማርክስ ብቻ ፈረንሳዊ ባሏ ጋር ተረጋግታ የኖረች ቢሆንም እኤአ1911ዓ/ም እራሷንና ባሏን ገድላ የማርክስን ቤተሰብ የህይዎት ታሪክ ቋጨችው። የካርል ማርክስ ስም ግን ገና ለሚመጡት ብዙ ዘመናት ከኮምዩኒዝም ጋር ጠቁሮ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል። በካርል ማርክስ አጓጊ ግን እውን መሆን የማይችል ፍልስፍና ምክንያት በዓለም ዙሪያ በትንሹ መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ህዝብ ለሞት ተዳርጓል።ሂውማን ራይትስ ዋች እና አምንስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ከ500,000 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመት ሰው መሞቱን ይገልጻሉ።

Copyright ©2019 TEAM | Powered by Networks for a Free Society.

One Comment on “ካርል ማርክስ እና ሶሻሊዝም

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s